በፖላንድ እንዲሁም በምስራቅ አውሮፓ የመጀመሪያው የሆነዉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ፡ክርስቲያን በእግዚአብሄር ፈቃድ የጀርመንና አከባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዲዮናስዮስ በተገኙበት በመጋቢት/፳፩፭ , March/2023 በዋርሶው ከተማ ቅዳሴ ቤቱን አከበረ
ስለ ቤተ ክርስቲያናችን
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጥንታዊትና ሐዋርያዊት የሆነች በሐዋርያት ሥራ ምዕ 8፡26-38 ላይ እንደተመዘገበው ጌታችንና መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከ0ረገ ፩ አመት ሳይሆነው በ34 ዓ.ም በጃንደረባዋ ቅዱስ ባኮስ ክርስትናን የተቀበለች ቀደምት ቤተ ክርስቲያን ናት። ቤተ ክርስቲያኗ በ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የመንግሥት ሃይማኖት የሆነችና እና ቅዱስ ሲኖዶሷም ከ328 ዓ.ም ጀምሮ በአዋጅ አገልግሎቱን መስጠት የጀመረባት ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን ናት።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሐዲስም ሆነ በብሉይ ኪዳን የተመሰከረላት በሐዋርያዊ ሰንሰለት ላይ የተመሰረተች እምነት ስትሆን፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከኦሬንታል ኦርቶዶክስ እህት አብያተ ክርስቲያናት ጋር በመሰረታዊ የሃይማኖት አስተምህሮ (ዶግማ) ትስማማለች፣ የጋራ እምነትም ትጋራለች።
በፖላንድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መደበኛ እና ይፋዊ መንፈሳዊ አገልግሎቷን የጀመረችው ከአራት ዓመታት በፊት ማለትም በ2020 እ.ኤ.አ ነበር። ለዚሁ መንፈሳዊ እንቅስቃሴ መጀመር ምክንያት የሆነው ለትምህርት እና ሙያዊ ሥራ ወደ ፖላንድ የሚገቡ ወጣት ኢትዮጵያውያን ምእመናን ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ ነው። ቋሚና ተስማሚ የመሰብሰቢያና የአምልኮ ቦታ ባለመኖሩ ምክንያት ለመጀመሪያዎቹ ሁለት ዓመታት ያክል መንፈሳዊ አገልግሎቶችን በተለያዩ(ተለዋዋጭ) ቦታወችና በበይነ መረብ የመገናኛ ዘዴዎች ሲካሄዱ ቆይተዋል። ነገር ግን ከ2022 እ.ኤ.አ መጨረሻ ጀምሮ በምስራቅ ኦርቶዶክስ የመላው ፖላንድ ሜትሮፖሊታን ፣ የዋርሶ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳቫ፣ እና ምዕመናን በጎ ፈቃድና ድጋፍ፣ ዋርሶ በሚገኘው የፖሊሽ ኦርቶዶክስ ፣በቅድስት ሃጊያ ሶፊያ ቤተ ክርስቲያን ፣ ፑዋቭስካ 568 (Pulawska, 568) ለአገልግሎት የሚሆን ቦታ ማግኘት ተቻለ።
ከዚህም በኋላ በመጋቢት 2023 እ.ኤ.አ የምስራቅ ጎጃም እና የጀርመን እና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዲዮናስዮስ በተገኙበት፣ በብጹዕነታቸዉ ቡራኬ እና መልካም ፍቃድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በፖላንድ አገልግሎቷን በይፋ ጀምራለች። በሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል ስም የተሰየመችው ቤተ ክርስቲያን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ወርሃዊ የቅዳሴ፣ ተጨማሪ ወርሃዊ የጸሎት፣ የዝማሬ እና የትምህርት መርሐ ግብራትን በማከናወን ላይ ትገኛለች። ቤተ-ክርስቲያኒቱ የተለያዩ መንፈሳዊ በዓላትን በድምቀት የማክበር እና የመንፈሳዊ ጉዞዎችን ማዘጋጀትን የመሳሰሉ መንፈሳዊ አገልግልቶችን እየሰጠች ትገኛለች። ምንም እንኳን አብዛኛዉ ምዕመን ተማሪ ቢሆንም፣ ከሁለት መቶ በላይ የሚቆጠሩ ምዕመናን በስሯ ይገኛሉ።
በአሁኑ ጊዜ ቤተክርስቲያኗ ከፖላንድ መንግስት እውቅናና ፍቃድ ለማግኘት አስፈላጊ ሰነዶችን በማሟላት ላይ የምትገኝ ሲሆን በተመሳሳይ ሁኔታም በቋሚነት ለአገልግሎት የሚውል ሕንጻ ቤተ-ክርስትያን ለማግኘት ጥረት እየተደረገ ይገኛል፤ ይህም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በፖላንድ ሀገር ውስጥ ዘላቂ ህልውናዋን ለማረጋገጥ ታላቅ መሰረት ይሆናል።